የታዳጊዎችና ወጣቶችን የፈጠራና ክህሎት አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የታዳጊዎችና ወጣቶችን የፈጠራና ክህሎት አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ የሆነ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት የታዳጊዎችንና የወጣቶችን የፈጠራና የክህሎት አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ4ኛው ዙር ሰመር ካምፕ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶችን አስመርቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የሠላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፣ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዲጂታል ዘመን ወቅቱን የዋጀ በክህሎት መር እውቀት የሠለጠነ ዜጋን ማፍራት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይበር ደህንነት እና ዘመኑ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ እውቀት የታጠቁ ወጣቶችን በተከታታይ የማሰልጠንና የማሰማራት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት በሰው ኃብት ልማት በተለይ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል እያደረገች ላለው ሽግግር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው ብለዋል።
የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ዋና ዓላማ በዘርፉ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎት በማሳደግ እና በዘርፉ ለሀገር የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ወቅቱን የሚመጥን ብቁ፤ ዕውቀት እና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሳይበር ታለንት ስልጠና አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።