በዞኑ በመኸር አዝመራ የለማ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥና የጥራጥሬ ምርት ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በመኸር አዝመራ የለማ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥና የጥራጥሬ ምርት ለማእከላዊ ገበያ ይቀርባል
ገንዳውኃ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር አዝመራ የለማ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥና የጥራጥሬ ምርት ለማእከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌትነት በሊሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ዞኑ ያለውን ተስማሚ ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት በመጠቀም ገበያ ተኮር ምርቶችን በስፋትና በአይነት ማልማት ተችሏል።
በዚህም በመኸር አዝመራ ከለማው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ማሾ ምርት ለማእከላዊ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደ ማዕከላዊ ገበያ ከሚቀርበው ምርት ውስጥም 800 ሺህ ኩንታል የሚሆነው የሰሊጥ ምርት ሲሆን ቀሪው ደግሞ የአኩሪ አተርና ማሾ ምርት መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ በሚገኙ አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማውን የገበያ ተኮር ሰብል በጥራትና ከብክነት በጸዳ መንገድ እንዲሰበስቡ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ የሚመረተው የሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ማሾ ምርት ለህገ ወጥ ንግድ እንዳይጋለጥ ከአምራቾች፣ ነጋዴዎችና አቅራቢዎች ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመው ቁጥጥሩም ይጠናከራል ብለዋል።
በዞኑ የመተማ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት ጌታው መለሰ በመኸር አዝመራ ያመረቱትን 35 ኩንታል የሰሊጥና የአኩሪ አተር ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርታቸው ለማእከላዊ ገበያ እንዲቀርብም ከብክነት በጸዳ መንገድና በጥራት እየሰበሰቡ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚሁ ወረዳ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ አህመድ ኑሩ በበኩላቸው ከአምራቹ አርሶ አደር ለማእከላዊ ገበያ የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በተሻለ ዋጋ መግዛት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በዚህም እስከ ሶስት ሺህ ኩንታል ሰሊጥና አኩሪ አተር በመግዛት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ አቅደው እየሰሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ባለፈው ዓመት በዞኑ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአኩሪ አተርና የሰሊጥ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉም ተገልጿል።