ቀጥታ፡

በሊጉ የመጨረሻ ቀን ውሎ ሲዳማ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ጋር ይጫወታሉ 

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 15/ 2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ዛሬ በሲዳማ ቡና እና ሃዋሳ ከተማ መካከል ይደረጋል። 

የክለቦቹ ጨዋታ ቀን 10 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። 

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ሲዳማ ቡና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን 4 ለ 1፣ ሃዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።

የዛሬው መርሃ ግብር ሁለቱ ቡድኖች በማሸነፍ መንገድ ለመቀጠል የሚያደርጉት ፍልሚያ ይሆናል። 

ቡድኖቹ በ2017 ዓ.ም በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሃዋሳ ከተማ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

አምና በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተገናኝተው ሃዋሳ ከተማ በተባረክ ሄፋሞ ግብ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ዛሬ ሊያደርጉት የነበረው የሊጉ ጨዋታ መድን ከግብጹ ፒራሚድስ ጋር በሚያደርገው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም