ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ወራት ለኢነርጂ እና መስኖ አገልግሎት የሚውሉ ግድቦች ይመረቃሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 15/2018(ኢዜአ):- በሚቀጥሉት ወራት ለኢነርጂ እና መስኖ አገልግሎት የሚውሉ መካከለኛ እና ከፍተኛ ግድቦች እንደሚመረቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን አስመልክቶ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የመፍጠንና መፍጠር አስፈላጊነት በአሁኑ ሰዓት በግልጽ መታየት እየጀመረ ነው ብለዋል።

ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ያሉት በጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቦችን አስመልክቶ ባነሱት ሀሳብ ላይ በሶማሌ ክልል የመስኖ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ወልመል የመስኖ ልማት ግድቦችን በቅርቡ ከተመረቁ ፕሮጀክቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት ወራትም የመካከለኛ እና ከፍተኛ ግድቦች ተመርቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ ጠቁመው ግድቦቹ ለኢነርጂና ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የተመረቁ እና ግንባታቸው የተጠናቀቁ ግድቦች የመፍጠንና የመፍጠር አቅም ማሳያ እንደሆኑ ገልጸው መፍጠን፣ መፍጠር እና በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቀጣይ ለመመረቅ ወረፋ የሚጠብቁ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እንልፋ እንትጋ ከልፋታችን ውጪ የሚለወጥ ሀገር አይኖርም የሚለው እሳቤ ለዚህ ውጤት በእጅጉ አግዟል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም