የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በፈተና ውስጥ ሆነን የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ያሳየንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በፈተና ውስጥ ሆነን የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ያሳየንበት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በፈተና ውስጥ ሆነን የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ያሳየንበት ነው ሲሉ ሚኒስትሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ ውይይት አካሂደዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይቱ በሰጡት አስተያየት፤ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የብልፅግና ግልጽ ራዕይ እውን የሆነበትና ነባራዊ ሁኔታ ሲመች ብቻ ሳይሆን በፈተና ውስጥም የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬነት የታየበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከለውጡ መንግስት በፊት የቆመ ፕሮጀክት ነበር ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱን ስራ ማስቀጠል በማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንደነበር በማስታወስ በአመራር ቁርጠኝነትና ውሳኔ አሁን ላይ ነፍስ ዘርቷል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ ከኃይል ማመንጫነት ባለፈ ሌሎች በርካታ ትሩፋቶች እንደሚኖሩትም ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱን እንደገና ለማስጀመር የተደረገው የመጀመርያ ጉዞ አካል እንደነበሩ ያስታወሱት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በወቅቱ ቁጭትና የእንችላለን ስሜት ይንጸባረቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በመሆን ፕሮጀክቱ በቁርጠኝነት መጀመሩንና ፕሮጀክት መጀመር የሚያስችል አቅም ባልነበረበት ወቅት በፈተና ውስጥ የተጀመረ ፕሮጀክት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በቆራጥ አመራር ፕሮጀክቱ ህይወት ተዘርቶበት ለእዚህ በመድረሱ መደነቃቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለኢንዱስትሪ፤ ለግብርና እና ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ከሚኖረው ሚና ባሻገር የፖለቲካ፤ ዲፕሎማሲ እና ይቻላል መንፈስን የሚያሳይ መሆኑንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ሚናም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እውን እየሆኑ የሚገኙ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ መሰረት የሚጥሉ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ ለዜጎች የኩራት ምንጭ የሆኑና የሀገሪቱን አቅም ያሳየንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ፣ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች የተጠናቀቁና በመገንባት ላይ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ልማት በተግባር ተገልጦ እንዲታይና የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ሂደት ውስጥ አመራሩ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
የታዩትን አስደማሚ ውጤቶች ለማስቀጠልና የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ እንደሚሰሩም ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል፡፡