በፈተና ውስጥም ሆነን በዕይታ ለውጥ ሥራዎቻችንን እንሠራለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በፈተና ውስጥም ሆነን በዕይታ ለውጥ ሥራዎቻችንን እንሠራለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ፈተና ትናንትም ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል፤ እኛ ግን በዕይታ ለውጥ ሥራዎቻችንን እንሠራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።
ከግምገማው በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ሁኔታው አስቻይ ባልሆነበት፣ ብዙ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዴት ይሠራሉ? የሚሉ ጥቄዎችን በተደጋጋሚ እንደሚሰሙ አንስተዋል።
በፈተና ውስጥ ውጤት ስለማምጣት ለሚያስቡ ሰዎች ያለኝ መልዕክት፤ በመጀመሪያ ምቀኞች የሚያድግን ነገር ዕድገት አይገቱም ብለዋል።
ሰዎች በፈተና ውስጥ ዕድል ፈልቅቀው እያወጡ ካላወቁበት በቀር በፈተናና በምክንያት ታስረው የሚቆሙ ከሆነ ሀገርን መሥራት ሳይሆን ቤተሰብ ለመምራት ይቸገራሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።
ፈተና እየጨመረ እንደሚሄድ መገንዘብ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባደግንና ሀብታችን መውጣት በጀመረ ቁጥር አሁን የምናውቃቸው ፈተናዎች ብቻ ሳይሆኑ አዳዲስ ፈተናዎች ይወለዳሉ ብለዋል።
ፈተና እንደሚያጋጥመን ዐውቀን ማንኛውም ተግዳሮት ሲገጥመን እንደ ዕድል ወስደን ለመሥራት የማንዘጋጅ ከሆነ፤ ማንኛውም እንቅፋት እየመጣ ጠልፎ ሊያስቀረን ይፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።
ትላልቅ ሀገራት በልካቸው ፈተና አለባቸው፤ ያን ፈተና የሚያልፉት ግን ከእያንዳንዱ ፈተና ውስጥ ዕድል ማውጣት ይቻላል ብለው ሲያምኑ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ፈተና ትናንትም ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል፤ እኛ ግን በዕይታ ለውጥ ሥራዎቻችንን እንሠራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።