በኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የታየው የፕሮጀክት ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ለሌሎች የልማት ስራዎች ልምድ የሚወሰድበት ነው - ሚኒስትሮች - ኢዜአ አማርኛ
በኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የታየው የፕሮጀክት ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ለሌሎች የልማት ስራዎች ልምድ የሚወሰድበት ነው - ሚኒስትሮች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት የታየው የፕሮጀክት ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ለሌሎች የልማት ስራዎች ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ሚኒስትሮች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን አስመልክቶ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ሚኒስትሮች፤ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ራዕይ ሲኖር ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ እና የፕሮጀክት ቅልጥፍና እና ውጤታማነት ትልቅ እመርታ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በተደረገው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እጅግ ውጤታማ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
ሪፎርሙ በራስ አቅም ሀገራዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን በማካተት እየተተገበረ በመሆኑ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በማዕድንና በሌሎችም ዘርፎች የሚታይ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች እንዲሁም በገጠሩ አካባቢ የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች የህዝቡን አኗኗር በመቀየር አስደናቂ ለውጥ እያስገኙ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በሁሉም ዘርፍ በተፈጠረው ተጽዕኖና የቀጣናው እጣፈንታ ከኢትዮጵያ አቅም ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ያልነበራቸው ሀገራት ጭምር ግንኙነት እንዲኖራቸው መፈለጋቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ለሀገር ለሚያስፈልግ ነገር መትጋትና መከታተል ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ናቸው፤ የኮይሻ ግድብ ለዚህ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
ለግድቡ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በራስ አቅም ማምረት በመቻሉ ወጪና ድካምን መቀነስ ማስቻሉን መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሀገራቸውን የሚወዱ ሰራተኞችን መመልከታቸውን በማውሳት ይህም ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ለስልጠና አቅም መሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮይሻ ግድብን ለሁለተኛ ጊዜ መጎብኘታቸውን በመግለጽ አሁን በተመለከቱት አፈጻጸም መደነቃቸውን አንስተዋል፡፡
የቆመን ፕሮጀክት ነፍስ መዝራት መቻል ትልቅ የአመራር ክህሎትና ጥበብ የሚጠይቅና ይህም የታየበት ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ለግንባታ የሚውሉ ግብዓቶች በአካባቢው ከሚገኙ ሀብቶች የሚገኙ መሆኑ ያላየነው ብዙ ሀብት በእጃችን እንዳለ የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ እንደ መንገድና መብራት የመሳሰሉ የማህበራዊ አገልግሎቶች ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ሲሉ ሚኒስትሯ አንስተዋል፡፡
የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም እንደ ሀገር የተሻለ ስራ መሰራቱን የሚያሳይና የኮይሻ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ የፕሮጀክት ቅልጥፍና ውጤታማነት የታየበት መሆኑን ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል፡፡