ኢትዮጵያ ሁልጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች ነው - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሁልጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች ነው - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።
በግምገማው ላይ አስተያየት የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የኢትዮጵያ የ100 ቀናት እቅድ ሀገሪቱ ሁልጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉዞ የማይቆም እና ሁሌም ታሪክ የሚጻፍበት መሆኑን ጠቁመው ጉዞዋም ትናንት ከነበረችበት እየተሻለ እና እየተለወጠ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአደጉ ሀገራት ፕሬዝዳንቶች በ 100 ቀናት የሰሯቸው ስራዎች ዜና ሆነው እንደሚነገሩ የገለጹት በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ እናትዓለም መለሰ በአፍሪካ መሰል ተግባራት አለመለመዳቸውንና ለዚህም የአህጉሪቱ መሪዎች አያልሙም ካለሙም አይተገብሩም የሚል ትችት እንደሚሰነዘር ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በ100 ቀናት የሚነገር ታሪክ፤ መሬት የወረደ ሃሳብና ሃሳብን ከህዝብ ተጠቃሚነት ጋር ማቆራኘት የሚችል አመራር በመታየቱ ሀገር ታሪክ እየጻፈች ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዜጎች የሚኮሩበት ታሪክ በኢትዮጵያውያን እየተጻፈ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በሪፖርቱ የቀረበው የ100 ቀናት አፈጻጸም ለታሪክ የሚቀመጥና ለዜጎች የሚነገር ትርጉም ያለው መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታሪክ እየተጻፈባት ያለች ሀገር ናት ያሉት ሀላፊዋ ሀገሪቱ ገንዘብ የምትሰራ እና በተቋማት ገንዘብ የምትይዝ ሀገር ሆናለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሁሉ የምትነግረው ታሪክና አሰራር እንዳላት በ100 ቀናት አፈጻጸም ሪፖርቱ መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡