ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮይሻ ስመጣ ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት አላየሁም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮይሻ ስመጣ ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት አላየሁም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኮይሻ ስመጣ ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት አልነበረም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።
ከግምገማው በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ገለጻ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮይሻ ግድብ መኖሩን የሰማሁት ለሕዳሴ ግድብ 1 ቢሊየን ዩሮ ሳሊኒ በሦስተኛ ወገን አስወስኗል ተብሎ እንዲቀንስልን ከሱ ጋር ድርድር በማደርግበት ጊዜ ነበር ብለዋል።
ከዚያ በኋላም ሳሊኒን ጨምሮ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ወደ ኮይሻ ስንመጣ ካምፕ እንጂ ፕሮጀክት ዐላየንም፤ በወቅቱ አንድ ኪሎ ግራም ሲሚንቶ እዚህ ፕሮጀክት ላይ አልተጨመረም ነበር ብለዋል።
በአንጻሩ ለግድብ ሥራ የሚያግዙ ልል አፈሮች ለማውጣት መጠነኛ ቁፋሮ የተጀመረ ቢሆንም እሱም በገንዘብ እጥረት ቆሞ እንደነበር አንስተዋል።
ያኔ የፕሮጀክቱን ጠቃሚነት ከነገሩኝ በኋላ ወደ ጊቤ 3 በመሄድ ትስስሩንና አስፈላጊነቱን ዐየሁ፤ ተመልሰን ቢሮ ከገባን በኋላ ይህንን ጉዳይ እንዴት አድርገን ልናስጀምርና ልናሳካ እንደምንችል ተመካክረናል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማመጣጠን ከፍተኛ ሚና እንዳለው በማመን ፕሮጀክቱ እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፋቸውንም አውስተዋል።
ለግድቡ፣ ለስፒል ወይ እና ለፓወር ሀውስ ሥራ የሚውል 15 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ ልል አፈር ተዝቆ መውጣቱንም ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ኪዩቢክ ሜትር ኮንክሪት ተሠርቷል፤ ይህ የሆነው ደግሞ አብዛኛው ግብዓት ከአዲስ አበባ አካባቢ ብረትም በሀገር ውስጥ ከሌለ ከውጭ በማምጣት ነው ብለዋል።
አሁን የኮይሻ ግድብ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍታ በ17 ሜትር ዝቅ ብሎ በ128 ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያውያን የተደመረ ጥረት ውጭ ስለወሰንንና ገንዘብ ስለመደብን ብቻ ፕሮጀክት ማሳካት አይቻልም ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ፕሮጀክት ራዕዩን ተጋርተው የሚሠሩ ሙያተኞችና ሠራተኞችን ብሎም የሚጠብቀውን ሰላም ወዳድ ማኅበረሰብ ጭምር እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
ለዚህ ደግሞ በኮይሻ የተሳተፉ ባለሙያዎች፣ ሠራተኞች ፕሮጀክቱ የሚገኝበት አካባቢ ማኅበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የኮይሻ ፕሮጀክት ለቀጣይ ሥራዎች ዐቅም በሚሆን መልኩ በዕውቀት ሽግግር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።