ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዕድገት አይቀሬ መሆኑን አመላካች አፈጻጸሞች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፡- በሁሉም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ አፈጻጸሞች ስኬታማነት የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት አመላካች መሆናቸውን ሚኒስትሮች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።

ከግምገማው ጎን ለጎንም ኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ጨምሮ ጨበራ ጩርጩራ የዝሆኖች ዳና ሎጂን ጎብኝተዋል።


 

በዚሁ ወቅት የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በሰጡት አስተያየት፤ መሪነት ያለንን ዐውቀንና ፀጋችንን ለይተን ወደ ሀብትነት መቀየርን ይፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ጨበራ ጩርጩራን በማልማት ወደ ሀብትነት የመቀየር ሥራ መሠራቱን ጠቅሰው፤ ይህም አካባቢውን በማስተሳሰር እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

ከፍ ሲልም በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አመላክተው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመሪነት ጥበብን ተጠቅመው ካለን በመጀመር መርኅ እየሠሩ መሆናቸውን ያሳያል ነው ያሉት።


 

ከ100 ቀናት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፤ በሁሉም መስኮች ተስፋ የሚፈነጥቁ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የግብርናው ዕድገት ከሌሎች ዘርፎች ዕድገት ጋር ተሳስሮ በመሠራቱ ተስፋችንን መጨበጥ ጀምረናል ብለዋል።

የሕዳሴው ግድብ፣ የወልመል መስኖ፣ የማዳበሪ ፋብሪካ እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ተስፋችንን መጨበጥ መጀመራችንን ብሎም የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬነት አመላካች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

አፈጻጸሙ እንደሚያስረዳው የተቀመጡ ግቦች በስኬት እየተከናወኑ ነው፤ የግብርናው ዕድገትም በአርሶና አርብቶ አደሩ ኑሮ ሁሉ የሚገለጥ ሆኗል ነው ያሉት።

የተመዘገቡት ውጤቶች የተገኙት በፈተና ውስጥ መሆኑ ደግሞ ሀገራችንን ፈተና ሳይበግራት ስኬታማ ጉዞ ማድረግ መቻሏን እንደሚያሳይ አንስተዋል።

አዲስ የሥራ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን ዐይቻለሁ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሕዝብን በማሳተፍ ጀምሮ የመጨረስ ዐቅም እያደገ መምጣቱንም ታዝቤያለሁ ብለዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ስለኮይሻ እና ጨበራ ጩርጩራ በሰጡት ሐሳብ፤ ካለፈው ዓመት አንጻር ሥራው እያደገ መሆኑን ተመልክቻለሁ ነው ያሉት።

አዳዲስ መዳረሻዎች ተገንብተው ለኢኮኖሚ ማመንጨት ተደማሪ ዐቅም እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የነበራትን ፀጋ ለይቶ እና ዐውቆ ወደ ሀብት መቀየር ጊዜ ይፈልግ ነበር፤ አሁን ጊዜው ሆኖ ወደ ሀብት እንዲቀየሩ እየተደረገ ነው ሲሉም አመላክተዋል።

አሁን ላይ የቱሪዝም ሀብት እየሰፋ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በግንባታ ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የሰው ልጅ ሊጎበኛቸው የሚገባ መዳረሻዎች እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

ሀገር ያላትን ዐቅምና ፀጋ በመለየት እየተከናወኑ ባሉ አዳዲስ መዳረሻዎች እና በ100 ቀናት አፈጻጸም በሁሉም ዘርፍ ለተገኙ ስኬቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥበብ የተሞላበት አመራር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም