ቀጥታ፡

በማክሮ ኢኮኖሚውና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ የተገኘው ስኬት የሦስት ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፡- በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከ100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የኢኮኖሚ ዕድገት አዝማሚያዎች ጋር በተያያዘ የተገኘው ስኬት የሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ድምር ውጤት መሆኑን አስገነዘቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።

ከግምገማው በኋላም አቶ አደም ፋራህ ከ100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የኢኮኖሚ ዕድገት አዝማሚያዎች ጋር በተያያዘ አስተያየት ሰጥተዋል።

በዚሁ ወቅትም፤ በጂኦ ፖለቲካ ውጥረት፣ በኢ-ተገማች የታሪፍ ዲፕሎማሲ፣ በአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ ብሎም የተዳከመ ማክሮ ኢኮኖሚ ዐውድ በሚታይበት ሁኔታ በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ችለናል ብለዋል።


 

ለዚህ አመርቂ ውጤት ያበቃን የሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ ሲሉም ገልጸዋል።

የመጀመሪያው ከለውጡ ወዲህ የዕይታ ለውጥ(ፓራዳይም ሽፍት) ማምጣት መቻላችን ነው ብለዋል አቶ አደም ፋራህ በሰጡት አስተያያት።

ለስኬታችን ሁለተኛው ምክንያት የአመራሩ የማስፈጸም ዐቅም፣ ትጋትና ቁርጠኝነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ሦስተኛው የሕዝቡ፣ የግሉ ሴክተር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ እና ትብብር ማደግ መሆኑን አንስተዋል።

መንግሥት ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲያነሳቸው የነበሩትን፤ የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ውጤታማ የማድረግ፣ ከሰላምና ጸጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመሆን በሂደት እየተቃለሉ እንዲሄዱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ቀሪ ሥራዎችንም በቀጣይ ከሕዝቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መንግሥት ለመፍታት ርብርቡን እንደሚያስቀጥል በግምገማቸው ወቅት መገለጹን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም