የኮይሻ ግድብ የለውጡ መንግስት እንደ ሕዳሴ ግድብ የታደገው ፕሮጀክት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የኮይሻ ግድብ የለውጡ መንግስት እንደ ሕዳሴ ግድብ የታደገው ፕሮጀክት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):- የኮይሻ ግድብ የለውጡ መንግስት እንደ ሕዳሴ ግድብ ከታደጋቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን አስመልክቶ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት ከዓመታት በፊት የኮይሻ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ መሰረት ከመጣል ባለፈ አፈጻጸሙ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልነበር ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ያለበት የግንባታ ደረጃ ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍተኛ ለውጥ እንዳለው አመልክተዋል።
የኮይሻ ግድብ ከኤሌክትሪክ ማመንጨት ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት የሚሆኑ ስራዎች እንደተካተቱ ጠቁመው፤ ሎጆችን ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎችን ማከናወን የሚያስችሉ ተራራዎች እንዳሉ አንስተዋል።
የግንባታው ስራ በፍጥነት እየሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግድቡ 1ሺህ 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ኮይሻ ለየት ያሉ በርካታ ተራሮች የሚገኙበትና ትልቁ የኦሞ ወንዝ የሚፈስበት መሆኑን ገልጸው፤ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ከተጠቀመች የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ኮይሻ ግድብ የለውጡ መንግስት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከታደጋቸው ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ኮይሻ፣ ሃላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ከኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቱ ጋር ተዳምረው ቱሪዝሙን ማሳደግ የሚችሉ ጸጋዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለኮይሻ ግድብ ግንባታ መፋጠን ለሰጡት በሳል አመራርም አመስግነዋል።