ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች የሚገባትንም ስፍራ ትይዛለች -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞዋን በማሳካት የሚገባትንም ስፍራ ትይዛለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን አስመልክቶ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በለውጡ ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸው ስራዎች መካከል አንዱ ኢትዮጵያንና ጸጋዎቿን በሚገባ ማወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ብቃት እና አቅም በቅጡ መገንዘብ ሀገርን ለመስራት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ አቅምን የሚገልጡ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።


 

የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ እና ኮይሻ የሀገርን አቅም የገለጡና ውጤት የተገኘባቸው ስራዎች መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ሀገሩን የሚያውቅ እና በሀገሩ ክብር የሚሰማው ሰው ተግቶ ለመስራት እና እያንዳንዷን ቀን ለመለወጥ እድል አድርጎ እንዲወስድ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ያየነቻው ፈተናዎችና መከራዎች አጠንክረውን በበለጠ ጽናት ተግተን እንድንስራ እና ውጤት እንድናገኝ አድርገውናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ እንደምትበለጽግና የሚገባትን ስፍራ እንደምትይዝ ምንም ጥርጥር የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን ራዕይ ለማሳካት የእያንዳንዱን ዜጋ ጥረት እና ድካም እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

ተግተን ከሰራን በልጆቻችን ላይ ፍሬውን ለማየት ጊዜው ሩቅ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ በአንዳንድ መስኮች የተገኘው ውጤት ከተጠበቀው በላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

የተገኙ ውጤቶች በቀጣይ የሩብ ዓመታት በማስቀጠል ውጤቶችን ማላቅ ከተቻለ የኢትዮጵያን የኃይል ሽግሽግ የሚቀይሩ መሰረታዊ ጉዳዮች የሚከናወኑበት ዓመት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የተገኙ ውጤቶችን ለማጽናት በበለጠ ትጋት እና አቅም መስራት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም