የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መገናኛ ብዙኃን ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መገናኛ ብዙኃን ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር መገናኛ ብዙኃን ልዩነት ሊኖራቸው እንደማይገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ሥራ አስጀምሯል፡፡
የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ የወል ትርክትና ብልጽግና ላይ የጋራ አቋም ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ማፍራት ያለመ ነው፡፡
በምርጫ ጋዜጠኝነት፣ ውሃ፣ የአቬሽን፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሰላም ጋዜጠኝነት እና በሌሎች ሀገራዊ ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምር፣ ስልጠናና የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የመጀመሪያውን በምርጫ ጋዜጠኝነት ላይ የሚያተኩር ስልጠና ትናንት አስጀምሯል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዳሉት፤ ብሔራዊ ጥቅም የሀገርን ደህንነት፣ ዋስትና እና ቀጣይነት የሚመለከት አንኳር ጉዳይ ነው፡፡
ሀገራዊ ህልውናና ደህንነት፣ ዕድገትና ብልጽግና፣ ታሪኳንና አስተዋጽኦዋን የሚመጥን ተሰሚነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ የባህልና የፖሊሲ ነጻነት እና ማህበረሰባዊ ልማትና ተጠቃሚነት በሚሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባት የአንድ ሀገር ሰዎችን የሚመለከት መሆኑን በማንሳት፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ ለኢትዮጵያውን አዲስ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ለነጻነታቸው የከፈሉትን ዋጋ እና ለታላቁ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በአብነት አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ ገልጸው፤ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች በብሔራዊ ጥቅም ላይ አንድ ዓይነት አቋም በመያዝ ለህብረተሰቡ ግልጽና ገንቢ መረጃ ማቅረብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ የጋዜጠኞችን አቅም በመገንባት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ትልቅ ሚና መወጣቱን ገልጸው፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ስልጠና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ጋዜጠኞች በብሔራዊ ጥቅም ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገር ህልውናና ልማት ላይ በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነት መኖር እንደሌለበት ገልጸው፤ ስልጠናው በኢትዮጵያ ያሉ የሁሉንም መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ያሳተፈ ነው ብለዋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ ስልጠናውን በምርጫ ጋዜጠኝነት መጀመሩን አንስተው፤ ለሰልጣኞች ቀጣይ ስራቸው ጠቃሚ የምስክር ወረቀት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያና አሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ሀይሉ በሻህ፤ ጋዜጠኝነት መንግስትና ብሔራዊ ጥቅምን የለየ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚደራደር ጋዜጠኛ መኖር የለበትም ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ ተመስርተው የሚሞግቱ ደፋር ጋዜጠኞች እንደሚያስፈልጓት ገልጸዋል፡፡
መገናኛ ብዙኃን በመርህና በሙያዊ ሥነ ምግባር ታንጸው የሚሰሩት ዘገባ ፖሊሲ ማስቀየር እንደሚችል ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የጋዜጠኞችን አቅም በመገንባት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አማካሪ እና የልህቀት ማዕከሉ አስተባባሪ ታምራት ደጀኔ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በምትፈልገው ጉዳይ ሁሉ ሀገሩን ማገልገል፤ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም መቆም ከሁሉም ይጠበቃል።
ሁሉም ሙያ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም መቆም እንዳለበት ገልጸው፤ የልህቀት ማዕከሉ ሰልጣኞችም ለዜጎች ተጠቃሚነት ዘብ መቆም አለባቸው ብለዋል፡፡
ጋዜጠኞች ያገኙትን መረጃ ሁሉ ከማሰራጨታቸው በፊት ለሀገር የሚኖረውን ጥቅም ግምት ውስጥ አስገብተው መዘገብ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡