የመማር ማስተማር ሂደትን የተሳለጠ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመማር ማስተማር ሂደትን የተሳለጠ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-ተማሪዎችን በሥነ ምግባር ለማነጽና የመማር ማስተማር ሂደትን የተሳለጠ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ገለጹ።
በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ባለድርሻ አካላት ውይይት አድርገዋል።
ረቂቅ ደንቡ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጁን ለማስፈጸም የወጣ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ አዋኪ ድርጊቶችን በተቀናጀ ግብረ-ሃይል መከላከልን ታሳቢ አድርጓል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንዳሉት፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ ትምህርትን የሚያውኩ ጉዳዮችን አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል።
የልጆቻችን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በትምህርት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የመማር ማስተማሩን ሂደት የሚያውኩ ተግባራትን መከላከል የጋራ ሃላፊነት መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት ትምህርት ለአገራዊ ልማትና ብልጽግና ያለውን ቁልፍ ሚና በመረዳት ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለአብነትን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውን በሙሉ አቅም ማስተግበር የሚያስችል የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ መውጣቱን አስታውሰዋል።
በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ ደንብም አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችል ነው ብለዋል።
ረቂቅ ደንቡ መልካም ሰብዕና የተላበሰ ዜጋ በማፍራት ለትምህርት ጥራት የራሱን ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ረቂቅ ደንቡን ለማዳበር የባለድርሻ አካላት ግብዓት ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሳለጥና በስነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ ለማፍራት የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ታደሰ ጌጡ ፤ የደንቡ መውጣት ተማሪዎችን በሥነ ምግባር ለማነጽና የመማር ማስተማሩን ሂደት ማሳለጥ ያስችላል ብለዋል።
በረቂቅ ደንቡ ለመልካም ሥነ-ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ጉዳዮች በዝርዝር ሊቀመጡ እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አበበ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በትምህርት ቤት አካባቢ የሚፈጠሩ አዋኪ ድርጊቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው።
ተማሪዎች ከቤት ወጥተው ትምህርት ቤት እስኪገቡ በአካባቢያቸው አዋኪ ጉዳዮች የሚያጋጥማቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ ማድረጉንም ነው ያነሱት።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ የሺወርቅ አያና፤ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ድርጊቶችን የመከላከል የሁሉም ኃላፊነት በመሆኑ የደንቡ መውጣት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የአምስት ዓመት የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የረቂቅ ደንቡ መዘጋጀት ለዚህ አጋዥ ይሆናል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዋኪ ጉዳዮችን ለመከላከል የወጣው ደንብ በየደረጃው ያሉ ባለደርሻ አካላት እየተወያዩበት ሲሆን፤ ለፍትህ ሚኒስቴርና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይሁንታ ካገኘ በዚህ ዓመት ጸድቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።