ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት በሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት በሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው
ባህር ዳር ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት በትብብር በሚያከናውኑት ተግባራት የድርሻውን ሚና እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።
ከ11ኛው የጣና ፎረም ጎን ለጎን የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶች የተሳተፉበት መድረክ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተካሄዷል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየን (ዶ/ር) እንደገለጹት የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሏቸውን ስራዎች በትብብር እየከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ትላልቅ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተማሪዎችን በመቀበል ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል ።
የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ለማበጀት በሚከናወኑ ተግባራት የተጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት አካባቢያዊ እውቀትን በመጠቀም ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችላቸውን ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
መድረኩም አፍሪካ እንደ አህጉር፣ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ያላትን እውቀት ከመጠቀም አንፃር አይነተኛ ሚና ለመወጣት እድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ትስስሩን ከመምራትና እንደ አህጉር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል አንጻር ውጤታማ ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል ።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው መድረክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌን ጨምሮ ከሱዳን፣ ከሱማሊያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ፕሬዚዳንቶችና የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተሳትፈዋል።