ለአህጉሪቷ ለዘላቂና አስተማማኝ የምግብ ሥርዓት ግንባታ አባል ሀገራት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ለአህጉሪቷ ለዘላቂና አስተማማኝ የምግብ ሥርዓት ግንባታ አባል ሀገራት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-ለአህጉሪቷ አስተማማኝና ዘላቂ የምግብ ሥርዓት ግንባታ አባል ሀገራት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የውሃ እና የአካባቢ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡
በስብሰባው ላይ የአባል አገራት በግብርና፣ በእንስሳት፣ በዓሳ ሀብት፣ በገጠር ልማት፣ በውሃ፣ በአካባቢ እና በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፎች ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡
በስብሰባው የሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም የማላቦ አጀንዳ (እ.ኤ.አ 2014 እስከ 2025) መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፤ በመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚተገበረው የካምፓላ አጀንዳ (እ.ኤ.አ 2026 እስከ 2035) ጸድቋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አባል ሀገራት የራሳቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም የግብርና ግብዓቶችንና ምርጥ ዘርን መጠበቀ እንዲሁም ብዝሃ ህይወትን ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና የውሃ ኃብትን ከማሳደግ አኳያም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ልማት ኤጀንሲ - ኒፓድ የግብርና፣ የምግብ ዋስትና እና የአካባቢ ዘላቂነት ዳይሬክተር ኤስቴሪን ፎታቦንግ የካምፓላ አጀንዳ (2026–2035) በአፍሪካ የግብርና-ምግብ ሥርዓቶች ላይ የለውጥ ምዕራፍ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ከአጀንዳው ግቦች መካከልም ዘላቂ የምግብ ምርትን፣ አግሮ-ኢንዱስትሪያላይዜሽንን እና ንግድን ማጠናከር፣ ለግብርና-ምግብ ሥርዓት ለውጥ ኢንቨስትመንትና ፋይናንስን ማሳደግ ብሎም የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚሉ እና ሌሎችም ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ልማት ኤጀንሲ የካምፓላ አጀንዳ ስትራቴጂ እንዲሳከ ምቹ ሁኔታዎችን ሲያዘጋጅ መቆየቱንም ጠቁመዋል፡፡
የዩጋንዳ ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ እና የአምስተኛው የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የውሃ እና የአካባቢ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ተወካይ ፍሬድ ብዊኖ ክያኩላጋ የካምፓላ አጀንዳ የእንስሳት ሃብትን ማሳደግ ላይ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል፡፡
በዚህም ለእንስሳትና ለዓሳ እርባታ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ የእንስሳት መኖ ማሳደግ፣ ለእንስሳት ጤና እንዲሁም የዘረመል መሻሻልም ከትኩረት መስኮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
የካምፓላ አጀንዳ የአፍሪካ ግብርና ልማት መርሃ ግብር ታላላቅ ግቦች መሳካት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡