በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው 11ኛው የጣና ፎረም በስኬት መጠናቀቅ የክልሉ ከተሞች አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ አቅም ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው 11ኛው የጣና ፎረም በስኬት መጠናቀቅ የክልሉ ከተሞች አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ አቅም ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው 11ኛው የጣና ፎረም በስኬት መጠናቀቅ የክልሉ ከተሞች አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ አቅም ያሳየ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
ከዛሬ ጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው 11ኛው የጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው መድረክ ተጠናቋል።
በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ለሶስት ቀናት የሚመክር ይሆናል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር)፤ በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው 11ኛውን የጣና ፎረም ጉባኤ አስክመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።
የፎረሙ አስተባባሪ ኮሚቴ በአዲስ አበባና ባሕር ዳር ከተማ ለማካሄድ ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ ጀምሮ በክልል ደረጃ ኮሚቴ በማደራጀት ውጤታማ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኅይል ኮሚቴም ከፎረሙ ዋዜማ ጀምሮ በዕቅድ የተመራ ዝግጅት በማድረግ የተሳካ ስራ መስራቱንም ተናግረዋል።
በዚህም በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደው ፎረም በተደረገው ዝግጅት ልክ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የጣና ፎረም የባሕር ዳር ከተማ ተሳታፊ እንግዶችን ከአቀባበል ጀምሮ አጠቃላይ ሂደት ደስተኞች እንዲሆኑ ለማድረግ በትጋት ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።
11ኛው የጣና ፎረም ስኬት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል፣ እንግዳ ተቀባዩ የባህር ዳር ከተማ ህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በባሕርዳር ከተማ በስኬት የተካሄደው አህጉራዊ ፎረም የክልሉ ከተሞች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችን በብቃት ማስተናገድ እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።