ቀጥታ፡

''ጉዞ ወደ ሀገር ቤት''  የሚል የጉብኝት መርሃ-ግብር ሊካሔድ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ፣ ብዝሃ ሀብቷን ለማሳየትና ብሄራዊ ኩራትን ለማጎልበት እድል የሚፈጥር  ''ጉዞ ወደ ሀገር ቤት''  የሚል መርሃ ግብር ሊካሄድ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ገለጹ።

መርሀ ግብሩ ከዛሬ ጥቅምት 14 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሔድ ስለመሆኑም ተገልጿል። 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ሀገራዊ የጉብኝት መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

''ጉዞ ወደ ሀገር ቤት'' ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት በጉዲፈቻ የሄዱ ህጻናት ሀገራቸውን ባህላቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። 


 

በተጨማሪም ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩና ቀጣይነት ያለው ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያግዝ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ይሄው ለሰባት ቀናት የሚካሔደው የጉብኝት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃ ሀብት ለማስተዋወቅና ብሄራዊ ኩራትን ለማጎልበት እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጎብኝዎችን ለመሳብ እና አማራጭ የጉብኝት መርሃ ግብርን ለማዘጋጀት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፤ መርሀ ግብሩ በጉዲፈቻ ባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸው የህይወት ጥያቄ መልስ የሚያገኙበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።


 

አገልግሎቱ በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በቱሪዝም፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።


 

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በመዲናዋ የሚገኙ የተመረጡ የቱሪዝም መስህቦችን በማስጎብኘት በኩል ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።እንግዶች ያማረ ቆይታ እንዲኖራቸው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም