በባሕርዳር በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ580 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባሕርዳር በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ580 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው
ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፡- በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የበጋ ወቅት በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ከ580 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ።
መምሪያው የ2018 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ አካሄዷል።
የግብርና መምሪያው ኃላፊ አቶ የሰው ዘር ደመላሽ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ሌሎችንም ነዋሪዎች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዚህም በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከአምስት ሺህ 670 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት 580 ሺህ 113 ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ መቀመጡን ገልጸዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ለመስኖ ልማት የሚውል ሦስት ሺህ 271 ሄክታር መሬት በመለየት ከዚህ ውስጥ ከ72 ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን አንስተዋል።
በአጠቃላይ በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ሦስት ሺህ 300 ሄክታሩ በበጋ ስንዴ የሚሸፈን ሲሆን፤ እስካሁን 23 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት በስንዴ ለምቷል ብለዋል።
ምርታማነቱን ለማሳደግ የግብዓትና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማዋና በዙሪያው የሚገኙ ቀበሌዎች ለም መሬት፣ እምቅ የውሃ ሃብትና ታታሪ የሰው ሃይል ባለቤት በመሆናቸው ይህንን በማቀናጀት እቅዱን ለማሳካት ይሰራል ነው ያሉት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ግብአትን ለማሟላት መስኖ ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም እንደ ስንዴ ያሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለአካባቢ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በስፋትና በዓይነት ለማምረት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን፤ የበጋ መስኖ ልማት ስራ ቅንጅትና ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል።
በዘንድሮው በጋ የሚካሄደውን የመስኖ ልማት ለማሳካትም አመራሩ፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ ተቀናጅተው መረባረብ እንዳለባቸው አሳሰበዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የከተማ አስተዳደሩ ፣ በዙሪያ ቀበሌዎች የሚገኙ የግብርና አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።