ቀጥታ፡

ብሄራዊ ባንክ ሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞች መረጃ እንዲልኩ መመሪያ ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የግል እና የሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ አጠቃቀም ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።

ብሄራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 1359/2017 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባደረገው ምርመራ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የባንክ ደንበኞች በዋናነት የንግድ ድርጅቶችና ግለሰብ ነጋዴዎች ለንግድ ሥራቸው ተብሎ ከተከፈተው እና በሚመለከተው የግብር ሰብሳቢ ተቋም ካስመዘገቡት የባንክ ሒሳቦች ውጭ የግል የባንክ ሂሳባቸው ወይም የሶስተኛ ወገን የባንክ ሒሳብ ተጠቅመው የተለያዩ የንግድ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እየፈጸሙ መሆናቸውን ማረጋገጡን ገልጿል።

ይህ አሰራር ከግብር ሰብሳቢ ባለስልጣናት ቁጥጥርና ክትትል ለመሸሽ የሚደረግ ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ በዚህ አግባብ የሚፈጸሙ የፋይናንስ ግብይቶች እና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች የወንጀል ፍሬ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዙ ወይም የተገናኙ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁሟል።

እነዚህን መሰል ተግባራትን ለመግታት አስፈላጊው የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑንም ነው ያስታወቀው።

በመሆኑም የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነትና ታማኝነት እንዲሁም በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ደህንነት ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የግል ባንክ ሂሳቦችን ለንግድ እና ለሕገ-ወጥ ድርጊት የሚጠቀሙ ደንበኞችን አስመልክቶ አስፈላጊ መረጃዎችን በማደራጀት እንዲልኩ መመሪያ ማስተላለፉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም