የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ አሰባሰብ አቅም እንዲጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ አሰባሰብ አቅም እንዲጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ አሰባሰብ አቅም እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ገለጸ።
ድርጅቱ የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎትን ሥራ የሚያቀላጥፉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አገልግሎቱ ለፖለሲ አውጪዎች፣ ጥናትና ምርምር አድራጊዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግበዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተደራሽ እያደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በርከት ያሉ ጉዳዮች መረጃ የመሰብሰብ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ ሥራውን መከወን የሚያስችሉ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ያደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ተቋማቂ አቅምን ከማሳደግ ባለፈ በአገልግሎቱ የሚሰበሰበው መረጃ ጥራት እንዲሻሻል አወንታዊ ሚና እንደሚጫወቱም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ ከዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ጋር በአቅም ግንባታ ዙሪያም በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ መሰል ትብብሮች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም በጎ ተጽዕኖ ያለው ወጤት እንዲመጣ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ቢሮ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ጥራቱን የጠበቀ፣ ወጥና፣ ትክክለኛ የስታትስቲክስ መረጃ አለመኖር ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።
መሰል ትብብሮች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋርም ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
ድርጅቱ በተለይም በሥራ ስምሪትና ፍልሰት ላይ የሚሰራ በመሆኑ በመስኩ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ወጥና ትክክለኛ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚሁ ዙሪያ አገልግሎቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዓለም የሥራ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ቢሮ ቺፍ ቴክኒካል አማካሪ አይዳ አወል በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ከቁሳቁስ ድጋፍ በሻገር በድርጅቱ ስር ያሉ የስታትስቲኪስ ባለሙያዎች ለአገልግሎቱ ባለሙያዎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም የስልጠና መርሃ ግብር በመንደፍ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አብራርተዋል።
ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የስታትስቲክስ መረጃ መኖር ድጋፍ የሚሹ ቦታዎችን ለይቶ ድጋፍ ለማድረግ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑንም አስረድተዋል።