ቀጥታ፡

ዘመናዊ የጥበብ ማሳያዎቹ በኪነ ጥበብ ዘርፍ  አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለማቅረብ ተጨማሪ አቅም  ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-በመዲናዋ የተገነቡና ዕድሳት የተደረገላቸው ዘመናዊ የጥበብ ማሳያዎች አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በማቅረብ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ተጨማሪ  አቅም የፈጠሩ መሆናቸውን የተለያዩ  የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የተገነቡ የጥበብ ማሳያዎች፣ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ኮምፕሌክስ እንዲሁም አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ይታወቃል።


 

በከተማዋ አዲስ የተገነቡና ዕድሳት የተደረገላቸው ነባር ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ለከተማዋ ነዋሪዎች አማራጭ የመዝናኛ ስፍራ ከመሆን ባለፈ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ ናቸው።


 

የቴአትር ደራሲና ባለሙያዋ አለም ፀሐይ እጅጉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በከተማዋ አዲስ የተገነቡና እድሳት የተደረገላቸው ዘመናዊ የጥበብ ማሳያዎች የባለሙያዎችን የፈጠራ ችሎታ በማዳበር ለኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪው መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

የጥበብ ማሳያ መድረኮቹ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የሚያንፀባርቁና አብሮነትን የሚያጎለብቱ የጥበብ ሥራዎችን በስፋት እንዲሰሩ ያግዛል ነው ያሉት። 

ኮምፕሌክሶቹ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገር በቀል ትውፊትን የሚያሳዩ የጥበብ ስራዎችን እንዲያቀርቡ የሚያስችሉ መሆናቸውን የገለጹት የቴአትር አዘጋጅ  የሆኑት ራሔል ተሾመ ናቸው።


 

የኪነ ጥበብ እድገት በባለሙያው የሚወሰን በመሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች ስራቸውን የሚያሳዩበት ቦታ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኬሮግራፊ ወይም የውዝዋዜ ባለሙያ የሆነው ጌታሁን ስሜ፤ ቀደም ሲል የነበሩ ሲኒማና ቴአትር ቤቶች ውስንነት የነበረባቸው ፣የጥበብ ስራን ለማቅረብ የማይመቹና ፣የባለሙያውንና የህዝቡን ፍላጎት የማያሟሉ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡


 

አዲስ የተገነቡት የጥበብ ማሳያ ስፍራዎች አለም አቀፍ የፊልም አውደ ርዕይን ጨምሮ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ስራዎችን  ማስተናገድ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጿል።

የቴአትርና የፊልም ባለሙያው ተስፉ ብርሃኔ በበኩሉ፤ ሲኒማ ቤቶቹ ለተመልካች ብቻ ሳይሆን ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች  አመቺ ምህዳር የፈጠሩ ናቸው ብሏል።


 

የቴአትር ጥበብ ባለሙያ እና መምህር እዮብ ገረመው እንዳሳሰቡት፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል። 


 

ሲኒማ እና ቴአትር ቤቶቹ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት መነሳሳትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን የተናገረው የቴአትርና የፊልም ባለሙያው ተስፉ ብርሃኔ ነው።

የኬሮግራፊ ባለሙያው ጌታሁን ስሜ በበኩሉ የህዝብን አንድነትና ሰላም የሚያረጋግጡ የጥበብ ስራዎችን መስራት የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ይገባል ብሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም