በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የባዮ ኢነርጂ ልማት እና የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የባዮ ኢነርጂ ልማት እና የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የባዮ ኢነርጂ ልማት እና የታዳሽ ኃይል ልማትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ የባዮ ኢነርጂ ልማት ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተደርጓል።
ስምምነቱን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ጌታቸው እና መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ያደረገው ሰንበርድ ባዮ-ኢነርጂ አፍሪካ ስራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ቤኔት ተፈራርመውታል።
ሰንበርድ ባዮ-ኢነርጂ አፍሪካ በአህጉሪቱ ግዙፍ የባዮ-ፊውል አምራች ኩባንያ ነው።
ኩባንያው ግብርናን መሰረት ያደረገ የባዮ ኢነርጂ ልማት፤ የአቪዬሽን ነዳጅ፣ ለትራንስፖርት የሚሆን ታዳሽ ኃይል፣ ለምግብ ማብሰያ የሚሆን ባዮ ፊውል ያመርታል ተብሏል።
የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል አማራጭ ላይ የጀመረችውን ስራ የበለጠ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ጌታቸው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዘላቂ የኢነርጂ ልማት የሚያጠናክር ነው።
ስምምነቱ ከውጪ የሚገባውን ነዳጅ ለመቀነስና የኢነርጂ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የግብርና ልማትን ለማገዝ፣ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን የኢነርጂ ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የሰንበርድ ባዮ-ኢነርጂ አፍሪካ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሪቻርድ ቤኔት በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ልማት ውጤታማ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በዛምቢያና ሴራሊዮን በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ላይ መሰማራቱን አስታውቀው ያለውን ልምድ በመጠቀም በኢትዮጵያ ውጤታማ ስራ እንደሚያከናውን አረጋግጠዋል።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ከድልማግሥት ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ስምምቱ በሀገሪቱ ከብክለት የጸዳ ትራንስፖርት ለመተግበር እየተደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።