ቀጥታ፡

በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለተማሪዎች ምገባና ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት ተሰጥቷል  

ኮምቦልቻ/ጎንደር ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ለተማሪዎች ምገባና ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም መድረክ በደሴና በጎንደር ከተሞች እያካሄደ ነው። 


 

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ በኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማስጠበቅ ለተማሪዎች ምገባ፣ ለግብዓት አቅርቦትና ትምህርት ቤቶቹን ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል።


 

የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ የጸጥታ ችግር ተከስቶ በነበረባቸው አካባቢዎችም ትምህርቱን ለማስቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር መሰራቱን ገልጸዋል።

ከግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በመማሪያ መጻህፍት ላይ የሚስተዋለውን እጥረት ለማቃለል የመጻህፍት ህትመት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሐገር ሽማግሌዎችና የወላጆች ተሳተፎን ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱንም አቶ መኳንንት አክለዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አለምነው አበራ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በትምህርት ዘመኑ ከ458 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።


 

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ በተካሄደ መድረክ ላይ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ እንደገለጹት በክልሉ በትምህርት ዘመኑ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መጥተዋል።


 

ለዚህ ውጤት የትምህርት አመራሩ፣ የወላጆች፣ የመምህራን፣ የክልሉ መንግስትና ህብረተሰቡ በቅንጅት መስራታቸው  የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው በእውቀትና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እድገት ለማስመዝገብ ትውልድ ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


 

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከ132 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት አቅዶ አብዛኛውን ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ልጆች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆን የለባቸውም በሚል ቁጭት ወላጆች ቁርጠኛ አቋም ወስደው እየሰሩ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ ናቸው፡፡


 

በዚህም በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ወደትምህርት ገበታ ለማምጣት ተችሏል ብለዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ከአማራ ክልልና ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም