የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ማዳረስ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ማዳረስ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዋሻ ሰባት፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክት አተገባበርና በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ላይ በአፋር ክልል ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ገጠራማ የሆኑ የአገሪቷን ክፍሎች የኤሌክትሪክና ብርሃን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በተለይም በገጠር ለሚገኙ ማህበረሰቦች "ሶላር ሆም ሲስተም" የተሰኘ ፕሮጀክት አማካኝነት ኤሌክትሪክ ተደራሽ በማድረግ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታቅዶ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለኢነርጂ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስና የብልፅግና ጉዞን እውን ለማድረግ የኢነርጂ አስፈላጊነት እሙን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት የኢነርጂ እምቅ ሃብት ውስጥ ከጂኦተርማል 10 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ ሐይል 130 ኪሎ ዋት እንዲሁም ከፀሐይ ብርሃን በርካታ አቅሞችን ማግኘት የምትችል መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን የተጠቀምነው ከ5 በመቶ በታች ነው ብለዋል።
እንደ ሃገር የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነት ከ54 ከመቶ ያልዘለለና ከ57 ሚሊዮን በላይ ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተጠቃሚ አለመሆኑን አስታውቀዋል።
በሀገሪቷ በአብዛኛው የማህበረሰብ ዘንድ የኢነርጂ ምንጭ ማገዶ መሆኑን ገልፀው ይህ ደግሞ ተያይዞ በሚያስከትለው የምድር መራቋት፣ የአፈር መሸርሸርና የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ሚኒስቴሩ በተለይም ገጠራማና ሩቅ በሆኑ ስፍራዎች "የሶላር ሆም ሲስተም"ን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ በአፋር ክልል በሚገኙ 32 ወረዳዎችና በ51 የጤናና ትምህርት ተቋማት ላይ ተደራሽ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል ውሃና አነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ በበኩላቸው እንዳሉት ለውጡን ተከትሎ ሚኒስቴሩ በውሃ ሃብት አስተዳደርና በኢነርጂ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
በተለያዩ ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ለአብነትም በሶላር ቴክኖሎጂ ዘርፍ በዳሎልና አፍዴራ ወረዳዎች ተጨባጭ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም በተለይም በጤና እና በትምህርት ዘርፍ ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አቶ አህመድ አስታውቀዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በፕሮጀክቱ በ827 ወረዳዎች የኤሌክትሪክና ብርሃን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በስልጠናው በአፋር ክልል የሚገኙ የክልል፣ የዞንና ወረዳ ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።