በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 971 ቶን በላይ ዓሳ ይመረታል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 971 ቶን በላይ ዓሳ ይመረታል
ጋምቤላ፤ጥቅምት 14/ 2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ5 ሺህ 971 ቶን በላይ ዓሳ የሚመረት መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ አስተወቀ።
በክልሉ የዓሳ ሀብት ልማትን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳዳግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የጋምቤላ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክረምስ ሌሎ ለኢዜአ እንደገለጹት የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ የፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በክልሉ ያለውን ሰፊ የዓሳ ሀብት በአግባቡ በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
በክልሉ ከሚገኙት ወንዞች፣ ኩሬዎች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሐይቆች 107 የዓሳ ዝርያዎች መኖራቸውንና በዓመት ከ17 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት ማግኘት የሚያስችል አቅም መኖሩንም አክለዋል።
ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ዓመታት የዓሳ ሀብት ልማቱን በማዘመን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ ብዙ ትኩረት ባለመሰጠቱ ሃብቱ በሚፈለገው ልክ ሳይለማ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሌማት ትሩፋት መርሃግብሩ ለዘርፉ የተሰጠውን ልዩ ትኩረት በመጠቀም ሀብቱን በሚፈለገው ደረጃ በማልማት የዘርፉን ጥቅም ለማሳዳግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንና በዘርፉም ተጨባጥ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት 4 ሺህ 976 ቶን ዓሳ ለማምረት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 4 ሺህ 995 ቶን ማምረት መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰው፤ በዘንድሮው ዓመትም ከ5 ሺህ 971 ቶን በላይ ዓሳ ለማምረት ታቅዶ እተሰራ ነው ብለዋል።
እቅዱን ለማሳካትም ቢሮው ለዓሳ አስጋሪዎችና ለዓሳ ግብይት ማህበራት የዓሳ ማጥመጃ፣ የዓሳ ማቆያ ማቀዝቀዣዎችና ለምርት ማጓጓዣ ትራንስፖርት የሚውል የሞተር ጀልባ ግብዓቶችን እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ የተገነቡትን ሶስት የዓሳ ማቀነባበሪያና መሸጫ ማዕከላትን የተጓደሉ ግብዓቶችን በማሟላት ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ወይዘሮ ክረምስ ገልጸዋል።
በዓሳ ግብይት ከተሰማሩት ማህበራት መካከል ''የጉር'' ማህበር ተወካይ ወጣት ቺቢ ኡቡር በሰጡት አስተያየት ማህበሩ በአራት ወረዳዎች ከሚገኙ የዓሳ አስጋሪ ማህበራት የዓሳ ምርት በመረከብ ለክልሉና ለተጎራባች ዞኖች እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በቀጣይም ማህበሩ ወደ አዲስ አባበና ሌሎች አካባቢዎች የዓሳ ምርት ለማቅረብ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ስራ የሚያስፈለግ የጀልባ ትራንፖርትና ሌሎች ግብዓቶችን ከክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ቢሮ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።