ኢትዮጵያ ለጎርፍ አደጋ መከላከል የምታደርገው ጥረት የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለጎርፍ አደጋ መከላከል የምታደርገው ጥረት የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ ወሳኝ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ለጎርፍ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት የምታደርገው ጥረት የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኦሞ-ጊቤ እና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ውስጥ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የተፋሰስ ጥናት (Basin Level Study) ለማካሄድ ኤስ ደብሊው ኤስ (SWS) ከተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እና የኤስ ደብሊው ኤስ (SWS) ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ ጃያን ካርሎ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ጎርፍ በግብርና ሰብሎች፣ በወሳኝ መሠረተ ልማቶች፣ በሌሎች ንብረቶች እና በሰው ሕይወት ላይ ለሚያደርሰው አደጋ ዘላቂና ሳይንሳዊ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡
የጎርፍ አደጋን መከላከል የመንግስት ሀገር አቀፍ የትኩረት መስክ መሆኑን በማንሳት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ መከላከል የሚያስችል ውጤታማ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመከላከል ከዓለም ባንክ ጋር በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው ስምምነት የኢትዮጵያ የጎርፍ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኦሞ-ጊቤ እና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ የሚካሄደው የተፋሰስ ደረጃ ጥናት የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
የጥናቱ ዝርዝር ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ወሳኝ ግብዓት የሚሆኑ ጥልቅ ሳይንሳዊ መሰረት ያለው የመፍትሄ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡
የኤስ ደብሊው ኤስ (SWS) ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ጃያን ካርሎ በበኩላቸው፤ የጎርፍ አደጋን መቀነስ የሚያስችል መፍትሔ ለማበጀት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የኤስ ደብሊው ኤስ (SWS) ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጥናቱን በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚያጠናቀቅ ተገልጿል፡፡