ቀጥታ፡

ዘላቂ የጤና ፋይናንስን በማጎልበት ጠንካራ የጤና ስርዓት የመገንባት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ ዘላቂ የጤና ፋይናንስን በማጎልበት ጠንካራ የጤና ስርዓት የመገንባት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።

27ኛው የጤናው ዘርፍ አመታዊ ጉባዔ "ዘላቂ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ለጠንካራ የጤና ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የተጠናቀቀው ዓመት በጤናው ዘርፍ ቀጣይነት ያለው መሻሻል የታየበት ነው ብለዋል።

በተለይ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት፣ የእናቶችና የህፃናት፣ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር አበረታች ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

ለጤና ተቋማት መድሃኒትን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን በማሟላት ረገድ ስኬታማ ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

የተጠናከረና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት የተከናወነበት ዓመት እንደነበርም አንስተዋል።

የጤና ስርዓቱን አቅም እና የዲጂታል ጤና ፈጠራዎችን በማሳደግ በኩል አመላካች ስኬቶች የታየበት እንደነበርም ገልፀዋል።

በአዲሱ ዓመት ደግሞ ስኬቶችን አጠናክሮ ለመቀጠል ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚተገበር የጤና ዘርፍ የልማት ኢንቨስትመንት ዕቅድ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል።

በዓመቱ ፈጠራዊ ስልትን በመጠቀም የተጠናከረ ሀገር በቀል የሀብት ማሰባሰብ፣ የጤና ፋይናንስ ሪፎርም ትግበራ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን የማስፋት ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

ፍትሐዊ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤን ማስፋት፣ የተጀመሩ የጤና መሠረተ ልማቶችን ማጠናቀቅና ማስፋት እንዲሁም የመድሃኒት አምራቾችን ማበረታታትና ቁጥራቸውን ማሳደግ ላይ ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ፣ ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን ማስፋት ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።


 

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪ መስፍን መላኩ በበኩላቸው፣ የጀመረው የብልፅግና ጉዞ እንዲረጋገጥ ጤናማና ንቁ ዜጋ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የክልሉ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ፣ መሰረተ ልማትን በማስፋፋትና አስቻይ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

በክልሉ የግሉ ዘርፍ በጤናው መስክ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የማበረታቻ ስርዓቶች መዘርጋታቸውንም ጠቅሰዋል።

በጉባኤው የፌደራልና የክልል የጤና ዘርፍ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የአጋር አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም