ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ሽግግርን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ሽግግርን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ሽግግር ስኬታማ እንዲሆን ድጋፏን ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች።
ሁለተኛ የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል የኢንቨስትመንት እና የአጋርነት ፎረም በሴራሊዮን ፍሪታውን ተካሂዷል።
የሴራሊዮን መንግስት እና የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ በጋራ ያዘጋጁት ፎረም “የአፍሪካ ኢነርጂ ሽግግር እና አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ለማፋጠን ኢንቨስትመንትን ማሳደግ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኢነርጂ ዘርፍ መሪዎችና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
ሁነቱ በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስመንት ማሳደግና አረንጓዴ መር ኢንዱስትሪን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
ኢትዮጵያም በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታዳሽ ኃይል አማካሪ ተመስገን ተፈራ የኢንቨስትመንት ፎረሙ በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ሽግግርን እውን ማድረግ የሚያስችል ሀብት ለማሰባሰብ፣ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግና የግሉን ዘርፍ ድጋፍ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና የሚወጣ መድረክ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ሽግግርን እውን ለማድረግና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነች ተናግረዋል።
ሁለተኛ የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል የኢንቨስትመንትና የአጋርነት ፎረም እ.አ.አ በ2024 በኬንያ ናይሮቢ የተካሄደው የመጀመሪያ ፎረም ውጤቶችን ገምግሟል።
በናይሮቢ የተካሄደው ፎረም በተሳታፊ ሀገራት ለተለዩ የአንድ ጊጋ ዋት ገደማ የታዳሽ ኢነርጂ ፕሮጀክቶች መንግስታት፣ የፋይናንስ ተቋማትና ባለሀብቶች የ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት ለመስጠት ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የፎረሙ ተሳታፊ የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ አቅም እና ሀብቱን ጥቅም ላይ በማዋል መካከል ያለውን ልዩነት ለመሙላት ፋይናንስ ፈሰስ ለማድረግና ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።