ቀጥታ፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ያስፈልጋል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን መቀየር እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከአኗኗር ዘይቤ መቀየርና ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው እንደሚመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሽታውን አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ቢሆንም በርካታ ዜጎች በበሽታው መያዛቸውን የሚያውቁት ስር ከሰደደ በኋላ እንደሆነም ይጠቀሳል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል ይላሉ።

በዚህም በርካታ ሰዎች ለስኳር፣ ለካንሰር፣ ለደም ግፊትና ለተለያዩ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተጋለጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እየጨመሩ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አስቀድሞ ለመከላከል በተለያየ መልኩ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ ያነጋርናቸው የህክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ በአብዛኛው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከአኗኗር ዘይቤ መቀየርና ከአመጋገብ ጋር ተያይዘው እንደሚመጡ አስረድተዋል፡፡


 

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር ትንቢት የኋላሸት እንዳሉት፤ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል ተጠቃሚነትና ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት ለበሽታው አጋላጭ ናቸው፡፡

በመሆኑም እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።


 

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር መላኩ እንዳለ በበኩላቸው፤ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም