ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ወደ ስራ መገባቱን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዞኑ አስተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ በዞኑ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ በመስኖ የሚለሙ ቦታዎች የመለየት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በክረምት የዝናብ ወቅት የተደፈኑ የመስኖ ካናሎችን የመጥረግና የማስተካከል እንዲሁም የዝናብ ውሃን በተለያዩ አማራጮች የመያዝ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የደረሱ የመኸር ሰብሎችን በመሰብሰብ ፈጥነው የሚደርሱ የመስኖ ሰብሎች መዘራታቸውንና ለግብርና ዘርፍ አመራርና ባለሙያዎች በእቅዶች ላይ በቂ ግንዛቤ እና መግባባት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

በመንግስት ደረጃ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዞኑ እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል ብለዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ እያደገ የመጣ ልምድ መሆኑን ገልጸው አርሶ አደሩም በስፋት እያለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም እስካሁን የተሰሩ የተፋሰስ ስራዎችን የማስጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንዲያረጋግጡ አድርጎ የመጠቀም ስራ ጎን ለጎን እንደሚሰራም አንስተዋል።

ዞኑ ባለፈው ዓመት በመስኖ ልማትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልማት ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል።

ምርታማነት በሚፈለገው ልክ አለማደግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አለመስፋፋትን ጨምሮ የአርሶ አደሩ ህይወት ማሻሻል ላይ አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከዞን እስከ ቀበሌ በአንድ በኩል ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራ በሌላ በኩል ደግሞ የልማት ስራዎች ላይ በቅንጅት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም