ቀጥታ፡

በአማራ ክልል 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕርዳር፤ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ) ፡-  በአማራ ክልል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤  የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት የሚሰጠው በቅድመና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ገልጸዋል።

‎ለምገባ ፕሮግራሙ የክልሉ መንግስት በጀት መመደቡንና ሌሎች አካላትም ድጋፍ የሚያደርጉበት አቅጣጫ ወርዶ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

‎የፕሮግራሙ መተግበር የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሳይቀሩና ሳያሰልሱ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማስቻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

‎በአሁኑ ወቅት የምገባ ፕሮግራሙ በደሴ፣ በኮምቦልቻና በባህር ዳር ከተሞች መጀመሩን ጠቅሰው፤ በሌሎች ከተሞች፣ በዞኖችና ወረዳዎችም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

‎የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ አስራቴ በበኩላቸው፤ በዞኑ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን 200 ሺህ ተማሪዎችን  የምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

‎በአሁኑ ወቅትም በአራት ወረዳዎች የተማሪዎች የምገባ ተግባር መጀመሩን ጠቅሰው፤  የምገባ ፕሮግራሙ በሌሎችም የዞኑ አካባቢዎች እስከተያዘው ወር መጨረሻ   ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

‎በዞኑ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 152 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ የልየታ ተግባር መከናወኑንና ወደ ተግባርም እንደሚገባ  የገለጹት ደግሞ ‎የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጋልኝ ተገኘ ናቸው።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በትምህርት ዘመኑ 20 ሺህ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና በአሁኑ ወቅትም ተግባራዊ  እንቅሰቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም