በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራዊ የተደረገው ሪፎርም በዘርፉ ያለው አቅም እንዲያድግ አስችሏል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራዊ የተደረገው ሪፎርም በዘርፉ ያለው አቅም እንዲያድግ አስችሏል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባራዊ የተደረገው ሪፎርም በዘርፉ ያለው አቅም እንዲያድግ ማስቻሉን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ተግባራዊ የተደረጉ ሪፎርሞች ሀገራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅም እንዲያድግ አስችለዋል።
በዘርፉ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው፤ አዳዲስ እሳቤዎችና አሰራሮች መዘርጋታቸው በስራ ዕድል ፈጠራ መስክ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገርና በርቀት የሥራ ዘርፎች ለ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደን 96 በመቶ ያህሉን አሳክተናል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገርና በርቀት የሥራ ዘርፎች ከአምስት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
ዕቅዱን በተሟላ መልኩ ለመፈጸም የባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ሥራ ላይ ለማዋል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ዜጎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት በቂ ክህሎትና እውቀት እንዲጨብጡ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ አሰራር በመዘርጋት በርካታ ዜጎች ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ዜጎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች መፍታት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ዜጎች ለስራ ወደ ውጭ ከመጓዛቸው በፊት ተገቢውን ክህሎት እንዲጨብጡ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ሚኒስቴሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሥራ ሀሳብ ባንክ ሟቋቋሙን ገልጸው በዚህም በርካታ የሥራ ሀሳቦች ተሰብስበው በዲጂታል ፎርማት መቀመጣቸውን አስረድተዋል።
ባንኩ ምን ልስራ ብሎ ለሚነሳ ሰው በየዘርፉ መነሻ የሚሆኑ የሥራ ሀሳቦችን የያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከባንኮች ጋር ሰፊ ምክክር መደረጉን ጠቁመው ባንኮች በተለያዩ አማራጮች ፋይናንስ እንዲያቀርቡ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገርና በርቀት የሥራ ዘርፎች ከ671 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተገልጿል።