ቀጥታ፡

በሀገሪቱ የተገነቡና በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ቀጣይ የዕድገት ምሰሶዎች ናቸው - ምሁራን

ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የተገነቡና በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ቀጣይ የዕድገት ምሰሶዎች መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ብርሃን እያመነጨ፣ የንጋት ሐይቅም ዓሣ እየተመረተበት እና የቱሪዝም መስህብ ስፍራ እየሆነ መጥቷል።

በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ጋዝ ማምረት የሚችለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትም ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል።

በቀጣይ ደግሞ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፍና ዘመናዊ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም የቤቶች ልማት እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት መንግስት አቅዷል።

የእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሀገራዊ ፋይዳ ምን ሊሆን ይችላል ሲል ኢዜአ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራንን አነጋግሯል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህር ይስሐቅ ንጉሴ፤ ለአንድ ሀገር የምጣኔ ሃብት ዕድገትና ማንሰራራት የኢንዱስትሪ ልማት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ የሜጋ ፕሮጀከቶች ግንባታ በሀገር ላይ እመርታዊ ለውጥ የሚያመጡና የዕድገት ስፕሪንግ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የተገነቡ እና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ለዕድገትና ማንሰራራት ጽኑ መሰረቶች ይሆናሉ ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተገነቡና በግንባታ ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ መግባት ከምጣኔ ሃብት ያለፈ የዲፕሎማሲ ስኬትንና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናከር መሆኑን አንስተው፤ ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ተጨማሪ አቅምና የሀገር ዋነኛ የእድገት ምሰሶዎች ይሆናሉ ነው ያሉት።

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መገንባት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ መስፋፋትና ማንሰራራት ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ረገድ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራትና ስኬት ለእዚህ ጥሩ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም