በአዲሱ የዓለም ሥርዓት የአፍሪካን እጣ ፋንታ የሚወስን የተሻለ አቅጣጫ መተለም ይኖርብናል-አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ የዓለም ሥርዓት የአፍሪካን እጣ ፋንታ የሚወስን የተሻለ አቅጣጫ መተለም ይኖርብናል-አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦በአዲሱ የዓለም ሥርዓት የአፍሪካን እጣ ፋንታ የሚወስን የተሻለ አቅጣጫ መተለም ይኖርብናል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
ከዛሬ ጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው 11ኛው ጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ለሶስት ቀናት የሚመክር ይሆናል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ፎረሙን በከፈቱበት ወቅት፥ ፎረሙ ለዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች አህጉራዊ ምክረ ሀሳቦችን በመፍትሄነት ማመላከት የሚያስችል ነው።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስተማማኝ፣የበለጸገና የተረጋጋ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምኅዳር ለመፍጠር ጥረት ማድረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።
በአዲሱ የዓለም ሥርዓት የአፍሪካን እጣ ፋንታ የሚወስን የተሻለ አቅጣጫ መተለም ይኖርብናል ብለዋል።
የጣና ፎረም መድረክ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ለአፍሪካዊያን የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ለመጠቀም በሚቻልባቸው መንገዶች የራሱን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ወጣቶችን ፈጣንና ተለዋዋጭ የዓለም ጂኦፖለቲካ የቴክኖሎጂ ጥበባዊ የተጠቃሚነት አሰላለፍ ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል።
የጣና ፎረም በባሕር ዳር እንዲካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ የፌደራልና የክልል እንዲሁም አህጉራዊ ተባባሪ ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ተሳታፊ ሙያተኞች በአፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮችና በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ልምድና ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ዝግጅትም ተጠባቂ የፎረሙ የመርሃ ግብር አካል ነው።
በፎረሙ ላይ በመሪዎችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዩ መልዕክተኞች ምክክር እንደሚካሄድ ተገልጿል።