ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን የሰፈነው ሰላም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ አግዟል-የጉጂ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች

አዶላ፤ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦በጉጂ ዞን የሰፈነው ሰላም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ማስቻሉን የጉጂ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

በዞኑ የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸው ተመልክቷል፡፡

የጉጂ ሆኩ አባገዳ ገናሌ አጋ በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን አልምቶ ለመጠቀምና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት ይገባል ብለዋል።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተሳሳተ መንገድ የተከተሉ ወገኖች የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመጡ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በአካባቢያቸው በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን በመቀበል ሰርቶ ለመለወጥ ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ነው የገለጹት፡፡

ይህም የአካባቢውን ሰላም በማጠናከር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጉጂ አባገዳ አባል ኡዴሳ አጋ በበኩላቸው፥ ቂምና በቀልን ትተን በመቻቻልና በመረዳዳት ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ ቆመን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም በአካባቢያቸው ለህብረተሰቡ የሰላምን ዋጋ በማስተማርና የታጠቁ አካላትም የሰላምን መንገድ በመምረጥ ወገኖቻቸውን በልማት እንዲክሱ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት የጸጥታ አካላትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሰላምና መረጋጋት እየተጠናከረ መምጣቱ የአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየተሳለጠ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የመንግስትን የሰላም ጥሪና የአባቶችን ምክር ተቀብለው ወደህብረተሰቡ የተቀላቀሉ ታጣቂዎችም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ሌላው አባገዳና የሀገር ሽማግሌ አኖሌ ኖቶ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲፋጠን የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ በሰላም አስፈላጊነትና ችግሮችን በውይይት መፍታት ላይ ከማስተማር ጀምሮ ለዘላቂ ሰላም ከመንግስት ጋር በመቀራረብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግርዋል።

የዞኑ አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቦጌ ታፈሰ በበኩላቸው፥ መንግስት አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ እንደነበረና ዛሬም ማስቀጠሉን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን አባገዳዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዞኑን ህዝብ ያሳተፈ የሰላም ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የመንግስትን የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ከ200 በላይ ታጣቂዎችና ዘጠኝ አመራሮቻቸው የታሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡም የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ሌሎች ታጣቂዎች የበደሉትን ህዝብ ለመካስ የተሀድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ሁለንተናዊ የልማትና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በመፋጠን ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም