የአጣጥ-ሌራ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአጣጥ-ሌራ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው
ወልቂጤ፤ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ):-የአጣጥ-ሌራ የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቡታጀራ አካባቢ ግንባታ ፕሮጀክቶች ማኔጅመት ፅህፈት ቤት መሃንዲስ ኢንጂነር ታዬ ደመቀ እንዳሉት፤ የአጣጥ-ሌራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት 97 ኪሎ ሜትርን የሚሸፍንና ግንባታውም እየተፋጠነ ነው።
የመንገድ ግንባታውን በሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ ታስቦ በ2010 ዓ/ም የተጀመረ ቢሆንም በተቋራጩ የአቅም ውስንነትና ብልሹ አሰራር ሳቢያ መዘግየቱን ጠቅሰዋል።
ችግሩን በመገምገም ከተቋራጩ ጋር የነበረውን ውል በማቋረጥ ከሌላ ተቋራጭ ጋር ውል መገባቱን አንስተው፥የነበረበትን መዘግየት ማካካስ በሚያስችል መልኩ አሁን ላይ በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ38 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው የመንገዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ጠቁመው፥ በቀሪው ላይ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የውኃ መፋሰሻ ቱቦ ቀበራ እንዲሁም የፉካ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ኢንጂነሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም ከመንገዱ ጋር በተያያዘ ከሚገነቡት 10 ድልድዮች ስምንቱ ግንባታቸው መጠናቀቁን ገልፀው፥ለመንገድ ግንባታው የተመደበው 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት በፌደራል መንግስት መሸፈኑንም አብራርተዋል።
ኢንጂነር ታዬ የመንገድ ፕሮጀክቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ፣የስልጤና የሃዲያ ዞኖችን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎችን የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
የመንገዱን ግንባታ እያከናወነ ያለው የአለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ተቋራጭ የአጣጥ ማዞርያ ሌራ ፕሮጀክት ተወካይ አቶ ሚካኤል ደስታ በበኩላቸው፤የመንገዱ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱን ከተረከቡ ከ2015 ዓ/ም ጀምሮ በተሻለ ፍጥትና ጥራት ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮ ዓመት 70 በመቶ ለማጠናቀቅ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።