በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መስህቦችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ባሻገር ቋሚ የገቢ ምንጭ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መስህቦችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ባሻገር ቋሚ የገቢ ምንጭ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
ጥቅምት 14/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መስህቦችን ከማልማትና ከማስተዋወቅ ባሻገር ቋሚ የገቢ ምንጭ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የቱሪዝም ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ፋንታሁን ታደሴ ለኢዜአ እንደተናገሩት ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋት የመስህብ ሀብቶችን የመለየት፣ የማልማትና የማስተዋወቅ ስራዎች በሰፊው እየተሰራባቸው ይገኛል።
በዚህም በክልሉ አምስት የቱሪዝም መስመሮችን በመለየት በሀብቶቹ ዓይነትና ይዘት የአካባቢውን ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተደረገው እንቅስቃሴም ልማቱን ከማስፋት ባሻገር የቱሪስቶች ቆይታ እንዲራዘም በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2017/18 በጀት ዓመት በእያንዳንዱ ወረዳዎች አንድ አንድ መስህብን በመለየት በኢንሼቲቭ መልክ እየለማ እንደሚገኝ አንስተው በዚህም የተሻለ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
ዘርፉን በማሳደግ ቋሚ የገቢ ምንጭ ለማድረግ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ህዝቡ በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት እየተሳተፈ እንደሚገኝም አክለዋል።
በዘርፉ ልማቱን ከማስፋት ባለፈ በርካታ ዜጎችን የስራ እድሉ ተጠቃሚ በማድረግ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።
ደንበል ሀይቅ፤ አብያታ ሻላ፤ ላንጋኖ መዝናኛ ቦታዎችን ከማልመት ባሻገር በማስተዋወቅ ረገድም ሰፊ ስራ መሰራቱን በማሳያነት አንስተዋል።
በኢሉባቦርና በአካባቢው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራም የሶር ፏፏቴ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት።
በማስፋፈያ ልማቱ የአካባቢው ማህበረሰብ በኢኮኖሚውም በኩል ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለማህበራዊ መስተጋብርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
በቀጣይ ዘርፉን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማምጣት በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በፌዴራል መንግስት ድጋፍ የለሙት የወንጪ ሃይቅ የባሌ ተራሮችን ጨምሮ የሶፍኡመር ዋሻ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለክልሉ ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አቅም መጨመራቸውንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።