በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት ተከናውነዋል
ሐረር፤ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የክረምት መውጣትን ተከትሎ የሚከሰት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት መከናወናቸውን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ አብዱረሃማን እንዳሉት፤ የክረምት ወራት መውጣትን ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት እንደሚኖር ከግምት ያስገባ የመከላከል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡
በዞኑ በሽታው የሚከሰትባቸው ወረዳዎች ላይ እስከታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ በመዝለቅ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማከናወን መቻሉን እንደአብነት አንስተዋል።
እንዲሁም በዞኑ የወባ ስርጭት በስፋት ይታይባቸው በነበሩ እንደ ሐረማያ፣ ፈዲስ፣ ኩርፋ ጨሌና ቀርሳ ወረዳዎች ጤና ባለሙያውንና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ እና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን መድፈን መቻሉን አክለዋል።
የአጎበር ስርጭትና ሌሎች የቅድመ መከላከል ስራዎችም በተቀናጀ መልኩ መከናወናቸውንና ከዚህም ባለፈ በዞኑ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ቅንጅታዊ ስራ መከናወናቸውን አስረድተዋል።
የወባ በሽታ ከሚከሰትባቸው የሐረማያ ወረዳዎች አንዱ ሲሆን ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሽታውን አስቀድሞ የመከላከል ስራ መከናወኑን የተናገሩት የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጅብሪል አብዱቃድር ናቸው።
በወረዳው ባለፉት 3 ዓመታት ከ21 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበሮች ለማህበረሰቡ መሰራጨቱን የጠቆሙት ኃላፊው የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማፅዳት ስራ በትኩረት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ የቀርሳ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢዴሳ ሙሉጌታ በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እስከ ቀበሌ ድረስ የቤት ለቤት ክትትል በማድረግ ህብረተሰቡ የወባ በሽታን አስቀድሞ እንዲከላከልና ጤናውን እንዲጠብቅ ግንዛቤ የመስጠት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የክረምት ወቅት መውጣቱን ተከትሎ የሚከሰትን የወባ ስርጭትና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ መሰራቱን የገለፁት ደግሞ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የፈዲስ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ አልይ ናቸው።
በዚህም በወባና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች የሚያዙ ህሙማን ቁጥር መቀነሱን አስረድተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በወባ በሽታ የሰው ህይወት አለማለፉን ከዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።