ቀጥታ፡

የቦንጋ ከተማ ኮሪደር ልማት ለከተማዋ ውበት፤ለነዋሪው ምቾት የፈጠረ ነው

ቦንጋ፣ ጥቅምት 14/2018 (ኢዜአ)፦ የቦንጋ ከተማ ኮሪደር ልማት ለከተማዋ ውበት፤ ለነዋሪዎችም ምቾትና ጤንነትን በማጎናጸፍ ተግባራዊ ምላሽ የተሰጠበት የልማት ስኬት ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የከተሞች ኮሪደር ልማት ከአዲስ አበባ ጀምሮ በክልል ከተሞችም ዘመናዊና ስማርት ከተሞችን የመገንባትና የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ የመቀየር ዓላማ ሰንቆ እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የከተሞቹ የግንባታ ሥራ ከውበት ባሻገር ለወንጀል መከላከልና ለነዋሪዎች ደህንነት ታስቦ የካሜራ ቁጥጥር ጭምር የሚደረግባቸው በመሆኑ ለሰላማዊ ህይወትና በንጹህ አካባቢዎች ለመኖር ጭምር ፍቱን እየሆኑ ይገኛል።

በዚሁ መነሻነትም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት በተመለከተ ኢዜአ ነዋሪዎችንና የሚመለከታቸውን የሥራ ሃላፊዎች አነጋግሯል።

ከከተማዋ ነዋሪዎቹ መካከል አቶ አሻግሬ ኃይሌ እና አቶ መንገሻ ወልደማርያም፤ የኮሪደር ልማት ሥራ በከተሞች ዘመናዊ አኗኗርን ለመከተል ጽኑ መሰረት እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል። 

የቦንጋ ከተማ የኮሪደር ልማትም ለከተማዋ ውበት፣ ለነዋሪዎችም ምቾትና ጤንነትን በማጎናጸፍ በተግባር ምላሽ የተሰጠበት የልማት ስኬት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ የልማት ሥራው የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገዶችን ለይቶ መከናወኑ የትራፊክ አደጋን በመቀነስ በኩል ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መምህር ተስፋዬ ወንድማገኝ፤ ከኮሪደር ልማት ሀገርን ከማልማት ባለፈ የዜጎች የልማት ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ የመጣበት ሰው ተኮር ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ሥራውን አጠናክሮ ከማስቀጠል ባለፈ ትውልድ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሁላችንም አደራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል፤ የኮሪደር ልማት ሥራ የከተሞችን ከገጽታ ማሳመር ያለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

ልማቱ በከተሞች በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ለኑሮ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ከተሞችን ከመገንባት ባለፈ ነዋሪዎች በንፁህ ቦታ ኑረው ጤናቸውን ለመጠበቅ ያለመ ጭምር መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ልማቱ ጥራት፣ ፍጥነትንና ዘመናዊነትን መሰረት አድርጎ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ በ13 ከተሞች ልማቱ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኮሪደር ልማቱ ከተሽከርካሪና እግረኛ መንገድ በተጨማሪ የመንገድ ዳርቻ መብራት፣ የአረንጓዴና የመዝናኛ ስፍራዎችን አካቶ እንደሚከናወንም አመልክተዋል።  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም