በክልሉ ልማትን በላቀ ደረጃ በመፈጸም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ልማትን በላቀ ደረጃ በመፈጸም መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ ጥቅምት13/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልማትን በላቀ ደረጃ በመፈጸም መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከክልሉ አመራር አካዳሚ ጋር በመቀናጀት "ብቁ አመራር ለላቀ ውጤት" በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት ለአመራር አባላት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት አመራሩ የክልሉን እምቅ የልማት አቅም ወደ ውጤት በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ለዚህም በጊዜ የለም መንፈስ በመስራት፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን እውቀት ጨብጦ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት ለውጤታማነት ተግቶ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነቱን በማጠናከር በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማላቅና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይኖርብታል ብልዋል።
ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክትን በማስረፅ ለህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም አክለዋል፡፡
ችግሮችን በመፍታት ለላቀ ስኬት መትጋትና በአገልጋይነት ሥነ ልቦና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በስልጠናው ከተሳተፉት የክልሉ አመራሮች መካከል የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቀመርያ ረሻድ ስልጠናው የመልማት እይታን በማስፋት በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብት ወደ ውጤት ለመለወጥ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ስራን ለማከናወን መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው የአካባቢውን ፀጋዎች በመጠቀም የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻልበትን መንገድ ያመላከተ ነው ያሉት ደግሞ የየም ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ ናቸው።
በቀጣይም ማህበረሰቡን በማስተባበር በግብርናና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አዲስ አስተሳሰብ በመፍጠር ለላቀ ውጤት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በስልጠናው ላይ ከክልል እስከ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡