ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሻኪር አህመድ ተናገሩ።

ማህበረሰብ አቀፍ አደረጃጀቶችን በመዘርጋት ችግሮችን በራስ አቅም ለመሻገር የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር የሚያግዝ ውይይት ዛሬ በድሬዳዋ ተካሄዷል።


 

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ሻኪር አህመድ እንዳሉት፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሻገር እንደ አገር የተዘረጉ የልማት ኢንሼቲቮች በድሬዳዋም በመተግበር ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በአስተዳደሩ የገጠር ወረዳዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ በከተማው ደግሞ የተለያዩ የቢዝነስ ሃሳቦችን በመቅረፅ፣ ስልጠና፣ የገንዘብ ድጋፍና ብድር በማመቻቸት የተከናወኑ ስራዎች ብዙዎቹን ከተረጂነት ለማላቀቅ አስችለዋል ብለዋል።

በተለይም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሻገር የወረዳ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ባለሃብቶች፣ ማህበረሰቡ እና የቤተሰብ አቀፍ አደረጃጀቶችን በመዘርጋት የተሻለ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሱሌይማን አሊ በበኩላቸው የእርስ በርስ መደጋገፍ እና መረዳዳትን በማጠናከር ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም መሻገር የሚችል ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።


 

በዚህም የመጠባበቂያ እህል እየተከማቸና ከሠራተኛው እና ከአመራሩ ወርሃዊ ፈንድ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም 30 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰው አምና በደረሰ የተፈጥሮ ችግር ለተጎዱት ወገኖች በራስ አቅም ከተሰበሰበ እህል 2 ሺህ 140 ኩንታል ለመጀመሪያ ጊዜ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

የዛሬው ውይይትም እነዚህን ቀጣይ ስራዎች ለማሳካት መደላድል የተፈጠረበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የወረዳ አመራሮች እና ባለሃብቶች፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ተግባራትን ከዳር ለማድረስ ኃላፊነታቸውን በቁጭት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም