ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት እያረጋገጠ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም የምክር ቤቱ አመራሮች እና አባላት የኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስን የስራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።


 

በመርኃ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌና የምክር ቤቱ አባላት ተሳትፈዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጉብኝቱ የኢንዱስትሪዎቹን የስራ እንቅስቃሴ እና ያሉበትን ደረጃ ለመመልከት ዓላማ ያደረገ ነው።

ዕሴት የተጨመረበት ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ እና በብረታ ብረት ምርት ላይ የተሰማራው ኤ ኤም ጂ ሆልዲንግስ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተከናወነው ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ጥሪ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

አፈ ጉባኤው በጉብኝታቸው ራዕይ ያለው ምን መፍጠር እንደሚችል ተመልክተንበታል ብለዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን ውጤታማነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

የአምራች ዘርፉ የውጭ ምንዛሪን በማዳን እና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።

የዘርፉን እድገት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም