የድሬዳዋን እድገት የሚመጥን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋን እድገት የሚመጥን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ድሬደዋ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋን እድገት የሚመጥን ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስተዳደሩ ገለጸ።
ስዊፍት የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር ዛሬ በ58 ሚሊዮን ብር የገዛቸውን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ዘመናዊ ታክሲዎች ለአባላቱ ዛሬ አስረክቧል።
በርክክቡ ላይ ተገኝተው ታክሲዎቹን ያስረከቡት የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍና የድሬዳዋ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ሹክሪ አብዱረህማን ናቸው።
አቶ ኢብራሂም በወቅቱ እንዳስታወቁት፤ የድሬዳዋ ከተማን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የዚህ አንዱ አካል የሆነው የድሬዳዋን የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተደራሽና ዘመናዊ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ስራ መሳካት አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ እየተደረገ መሆኑን አንስተው ዛሬ ማህበሩ ያከናወነው በአርአያነት የሚጠቀስ ስራም የዚሁ እንቅስቃሴ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የአስተዳደሩ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ስራ አስኪያ ሹክሪ አብዱረህማን ዘመናዊ ታክሲዎቹ ከከተማው ዕድገት ጋር የሚጣጣም ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
በተለይም በድሬዳዋ አየር መንገድ የሚገኙትን የቆዩ ታክሲዎች በዘመናዊ ለመተካት አንድ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ማህበሩ በተመሳሳይ ስራ በህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘመናዊ ታክሲዎቹ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር፣ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ፣ ለነዳጅ የሚወጣን ሃብት በማስቀረት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማላቅ ረገድ ወሳኝ አበርክቶ እንዳላቸው በመጠቆም።