ቀጥታ፡

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመበልጸግ የምትከተለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተግባር ገልጧል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመበልጸግ የምትከተለውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተግባር የገለጠ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ከማውጣት ባለፈ የቀጣናውን ሀገራት በሀይል ያስተሳስራል፡፡

ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ሌሎችም ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ለቀጣናው ዕድገትና ትስስር ሚናዋን እየተወጣች ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሚል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብቻዋን የመልማት ፍላጎት እንደሌላት ገልጸው፤ ብሔራዊ ጥቅሟ ተጠብቆ ሌሎች እንዲለሙ አበክራ ትሰራለች ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኃይል ለማስተሳሰር ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ነጋችንን በጋራ ዕውን እናድርግ የሚል አቋም እንዳላት ጠቅሰው፤ የሕዳሴ ግድብ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር ለመልማት ያላትን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ስትገነባ በተፈጥሯዊ ሀብቷ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እንጂ ማንንም የመጉዳት ዓላማ የላትም ብለዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ በመሆኑ ውሃው ሀይል አመንጭቶ እንደሚሄድ እየታወቀ የውሃውን ፍሰት ይቀንሳል በሚል የሚቀርበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዘጠኙን የናይል ተፋሰስ ሀገራት አግልሎ ሁለት ሀገርን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገው የቅኝ ግዛት ውል ፈርሷል ያሉት አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር)፤ የቅኝ ግዛት ውሎች ላይ ተቸንክረው የቀሩ ሀገራት ወደ ቀልባቸው መመለስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በራሴ የተፈጥሮ ሀብት ሌሎችን ሳልጎዳ በፍትሐዊነት መጠቀም እፈልጋለሁ የሚል ግልጽ አቋሟን በተግባር ያሳየችበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር) እንደ ሕዳሴ ግድብ አይነት ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ አልፈው ለጎረቤት ሀገራት ይተርፋሉ ብለዋል፡፡


 

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና ለኬንያ ኤሌክትሪክ እያቀረበች መሆኑን ገልጸው፤ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጸጥታና ደህንነት፤ በንግድና ማህበራዊ ጉዳዮች በመተሳሰር ቀጣናውን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቷም ገልጸዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ አባል አበባው ደሳለው(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ተጠቃሚ የመሆን ተፈጥሯዊ መብት አላት ብለዋል፡፡


 

የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ያላትን ፍላጎት በግልጽ ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ የውሃውን ፍሰት እንደሚቀንስ የሚነሳው ሀሳብ ጉዳዩን የፖለቲካ አጀንዳ ለማድረግ እንጂ ፍሰቱን እንደማይቀንሰው በዘርፉ ምሁራን ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም