የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እውነታ ላይ አዲስ ምዕራፍ ፈጥሯል - አቶ አወሉ አብዲ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እውነታ ላይ አዲስ ምዕራፍ ፈጥሯል - አቶ አወሉ አብዲ
ክልል ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ፖለቲካዊ እውነታ በመቀየር አዲስ ምዕራፍ መፍጠሩን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤትና በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተዘጋጀው 46ኛው የጉሚ በለል ውይይት "የሕዳሴ ግድብ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን" በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ፤ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በእንባ፣ በላብና በደም መጠናቀቁን አስታውሰዋል።
በዚህም ግድቡ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን ያደረገ ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን ያሸጋገረ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን እውቀት፣ ሃብትና ጥንካሬ ተገንብቶ መጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ከፍታ ጠንካራ መሰረት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የግድቡ ስኬት የአሁኑ ትውልድ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ለሚያደርገው ጥረት አርአያ የሚሆን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ምልክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በፓን አፍሪካኒዝም ሀሳብ የሆነውን የይቻላል አመለካከት ማደስ ያስቻለ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማሲ ላይ በተሰራ ጠንካራ ስራ በሴራ የተሞሉ ተቃውሞዎችን በመረጃና በማስረጃ በማሸነፍ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረው ይህም በአፍሪካ በውሃ ላይ ያለውን ትርክት ሙሉ በሙሉ ለውጦ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ብለዋል።
የኦሮሞ ህዝብም ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ለግድቡ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አቶ አወሉ አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቂ የሃይል ምንጭ መፍጠር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የተፈጠረው የንጋት ሃይቅ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እየሆነ መምጣቱንም ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ፤ ፕሮጀክቱ አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ በማቀየር አፍሪካን ለልማት ማነሳሳት መቻሉን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የቻለው አመራሩና ህዝቡ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት እንደሆነ ተናግረው ግድቡ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያቆሙት የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያ የውሃ ሃብት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።