የፍትህ ሥርአቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ሥርአቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል-ቢሮው

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፍትህ ሥርአቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የፍትሕና የፖሊስ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና የፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ምርመራ ውጤታማነትና በቅንጅታዊ አሰራር ላይ በጋራ የሚመክሩበት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ዳንኤል በመድረኩ እንደገለጹት፣ በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት የወንጀል ድርጊት አቤቱታን ከመቀበል እስከ ፍርድ ተፈፃሚነት ደረጃ ባለው ሂደት የፖሊስና የፍትህ ተቋማት ሚና የጎላ ነው።
በየደረጃው ያሉ የፍትህና የፖሊስ ተቋማት ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር የሀገርና የክልሉን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ከወንጀል የመከላከልና የህዝብን ሠላምና ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
እነዚህን ሃላፊነቶች በሚፈለገው ደረጃ ለመወጣት እና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን በተቋማቱ ውስጥ ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይ የፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን ለማድረግ የፍትሕና የፖሊስ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ በእስካሁኑ ሂደት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢኖሩም በዐቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቋማት ላይ ከፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትና ቅንጅታዊ አሰራር ጋር በተያያዘ አሁንም ጥያቄዎች እየተነሱ መሆኑን ወይዘሮ ቤተልሔም አንስተዋል።
የፍትህ አስተዳደር ስርዓቱን ከብልሹ አሰራር የፀዳና ውጤታማ የማድርጉ ሥራ በአንድ አካል ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ የሁለቱን ተቋማት ትብብርና ቅንጅታዊ ሥራ ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
መድረኩ በየደረጃው ያሉ የፍትህና የፖሊስ ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር በማጎልበት የወንጀል ጥቆማ መቀበል፣ ቅድመ ማጣራት ሥራ እንዲሁም የምርመራና ክርክር ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
በመድረኩ በቅንጅታዊ አሰራር ላይ ቀደም ሲል የተስተዋሉ ጉድለቶችን ለይቶ ከማውጣት ባለፈ በቀጣይ ተቀናጅቶ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንደሚደረስ አመልክተዋል።
ሁለቱ ተቋማት የመግባቢያ ሰነድ ከመፈራረም ባለፈ የጋራ ዕቅዶችን አውጥተው ወደተግባር እንደሚገቡም ወይዘሮ ቤተልሔም ገልጸዋል።
ለወንጀል ምርመራ እና ክስ ዝግጅት ውጤታማነት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ የመወያያ ሰነድ በክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታመነ ታደሰ ቀርቧል።
በመድረኩ የክልሉ ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ሰብስቤ ሻዎኖን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።