ቀጥታ፡

የጉባ ብስራቶች ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት በማውጣት ወደ ሁለንተናዊ  ብልጽግና የሚያሸጋግሩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦በጉባ የተበሰሩት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት በማውጣት ወደ ሁለንተናዊ  ብልጽግና የሚያሸጋግሩ ናቸው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

የትናንት ቁጭት ማሰሪያና የመጭው ንጋት ማብሰሪያ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የግድቡን መመረቅ ይፋ አድርገው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ገደሉን ተሻግራን ገድል አትመናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡን መመረቅ ይፋ ካደረጉ በኋላ፤ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት በሰላሳ ቢሊዮን ዶላር የሚገነቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረዋል፡፡

በወቅቱ ከተበሰሩ ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክለር ሃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ አየር መንገድ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የቤቶች ልማት በዋናነት ይገኙበታል፡፡

የጉባ ብስራቶች ለሀገራዊ ብልጽግና እና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያላቸውን ፋይዳ በተመለከተ ኢዜአ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለፈተናዎች የማይበገር ህዝብ እና መንግስት መኖሩን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡


 

የጉባ ብስራቶች በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ እውን የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ይዟቸው የመጣ ትሩፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ኢንዱስትሪዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በሀይል አቅርቦት ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚፈታ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ወደ መገንባት እንድንሸጋገር ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የማዳበሪያ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና የማዳበሪያ ፍላጎትን ለመሙላት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የቢሾፍቱ አየር መንገድ ፕሮጀክትም አፍሪካን የበለጠ እርስ በእርስ ከማስተሳሰር ባሻገር የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው አመላክተዋል፡፡ 

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ የጉባ ብስራት ከህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ የመጣ በረከት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


 

እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡ 

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሞጋ አባቡልጉ ይፋ የተደረጉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የሃይል አማራጮችና የልማት ግቦች  የሚያሰፉ ናቸው ብለዋል፡፡


 

በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እና ወጪ ተጠናቅቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ ምክር ቤቱ ህጎችን በማውጣትና የፓርላማ ዲፕሎማሲዎችን በማሳደግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም