ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል- ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማ በመሆኑ አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክን ጨምሮ ሁሉም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በአመታዊ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የነበረውን ተሳትፎ በስኬታማነት ማጠናቀቁንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ዓመታዊ ስብሰባውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር ሰፋፊ ውይይቶች የተደረጉበት እና የኢትዮጵያን የልማት ተግባራት ለመደገፍም ቁርጠኝነታቸውን የገለጹበት መሆኑን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል ከአይ ኤም ኤፍ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም ከአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ምክትል ሃላፊ እና ከተለያዩ ዲፓርትመንቶች ጋር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከፍተኛ መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን አንስተዋል።

ከአለም ባንክ ጋር በተያያዘም ለኢኮኖሚ ሪፎርሙ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ እንዲሁም ባንኩ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ከባንኩ ፕሬዝዳንት፣ ከተለያዩ የኦፕሬሽን ሀላፊዎች እና ከአፍሪካ ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ጋር የተሳካ ውይይት መደረጉንም አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ በጤና፣ በትምህርት እና በሰው ሃበት ልማት እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ጨምሮ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ሪፎርሙ እና በኢኮኖሚ እድገት ውጤታማ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በተካሄዱ የተለያዩ የፓናል ውይይቶችም የኢትዮጵያ እድገት ለበርካታ ሀገራት ተምሳሌት ሆኖ የቀረበበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያገኘበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በከተማ እና በገጠር ልማቶች ላይ እየሰራችው ያለው ስራ ስኬታማ መሆኑ የታየበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የግሉን ዘርፍ ለማነቃቃት የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ በመሆናቸው ያለውን አጋርነት ለማጠናከርም መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል።

ዓመታዊ ስብሰባው በአጠቃላይ የልማት አጋርነትንና የሪፎርም ውጤቶችን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም